በደቡብ ክልል የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር የተጀመረው የለውጥ አሰራር መሻሻል አሳይቷል

የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ጉዬ በበኩላቸው በስራቸው በሚገኙ 19 ወረዳዎችና ሀዋሳን ጨምሮ በሁለት የከተማ አስተዳደሮች አዲሱ የለውጥ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል
ሃዋሳ, ጥር 5 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በደቡብ ክልል የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጎልበትና ለማጠናከር የተጀመረው የለውጥ አሰራር መሻሻል ማምጣቱን አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችና ባለጉዳዮች ገለጹ፡፡
ዘንድሮ በክልሉ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች የህግ ግንዛቤ የሚያሳድግ ትምህርት እንደሚሰጥም ተመልክቷል፡፡
የክልሉ ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል እንዳሻው ስመኖ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ተከትሎ የመጣው አዲሱ የውጤት ተኮር የምዘና ስርዓት ፕሮግራም በክልሉ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡
በዚህም ቀደም ሲል ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቢያነ ህግ፣ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ በተናጠል የሚያካሄዱትን የተበታተነ አሰራር በማስወገድ በአንድ ላይ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተለይ የምርመራና የክስ፣ የህግ ጥናት ረቂቅ ዝግጅትና ግንዛቤ መፍጠር፣ የጠበቆችና ሲቪክ ማህበራት ፍቃድ ውልና ምዝገባ ክትትል ከተገኙት ለውጦች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልከተዋል፡፡
በዚህም የፍትህ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ቀደም ሲል ከስድስት ወር በላይ የሚፈጀው አሁን በሰዓታት፣ በቀናት ቢበዛ እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ውሳኔ እያገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
ከወንጀልና ከፍትሃብሄር ክሶች ጋር ተያይዞ ንፁሃን እንዳይጎዱና አጥፊዎች እንዳያመልጡ የተቀመጠው ግብም ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፍትህ አካላቱ ተቀናጅተው መስራታቸው ፈጣን ፍትህ ለተጠቃሚው ለመስጠት ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም በአዲሱ አሰራር ከሶስት ዓመት በታች የሚያሳስሩ መለስተኛ የወንጀል ድርጊቶች በእርቅ እንዲፈቱ የተጀመረው ፕሮግራም ህብረተሰቡ ከልማት ስራዎቹ እንዳይገታ፣ አላስፈለላጊ የመዝገብ ክምችት እንዳይኖርና የፈፃሚዎችን ጊዜ ለመቆጠብ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ፍትህን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በተለይ ቀደም ሲል የነበረው የተዘዋዋሪ ችሎት ወደ ምድብ ችሎት በመቀየር እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ተደራጅተው አፋጣኝ ውሳኔና ምላሽ በመስጠት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ጉዬ በበኩላቸው በስራቸው በሚገኙ 19 ወረዳዎችና ሀዋሳን ጨምሮ በሁለት የከተማ አስተዳደሮች አዲሱ የለውጥ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ ምድብ ችሎቶች በአለታ ወንዶና በይርጋዓለም ዳሌ ተዘዋዋሪ ችሎት በመክፈት የመዝገብ ክምችቶችና ውጣ ውረዶችን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በሀዋሳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከተገኙት ባለጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የፍርድ ቤቶቹ አገልግሎት አሰጣጥ ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው፡፡
በተጨማሪም በክልሉ ዘንድሮ የህብረተሰቡን የህግ ግንዛቤ ለማሳደግ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተለያዩ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ትምህርት ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አመልክተዋል፡፡
ይህም ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮላቸው ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ የፍትህ ስርዓቱ እንዲጎለብትና እንዲጠናከር የህብረተሰቡ ተሳትፎና ግንዛቤ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር