በሃዋሳ ከተማ ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ተመረቁ



ሃዋሳ, ታህሳስ 27 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዝ ልማት የተሰማሩ ወጣቶች ሀገሪቱ ስራ አጥነትን በመቅረፍ ልማታዊ ባለሃብትን ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተሰማርተው ወደ ልማታዊ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ 16 ማህበራት መመረቃቸው ተገልጿል፡፡
የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የከተማውን ነዋሪ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በመቀየር በርካታ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ በከተማው ስራአጥነትና ድህነትን በመቀነስ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው አመራሩ ባለሙያውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ጥንካሬ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ማህበራቱ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲቀረፍ እንዲሁም ፍትሃዊ የሃብት አከፋፈልና አጠቃቀም በከተማው እንዲሰፍን እስካሁን ያበረከቱት አስተዋጽኦ አበረታች እንደነበር አስታውሰው ኪራይ ሰብሳቢነት በልማታዊ አስተሳሰብ እንዲለወጥ ጠንክረው ሊሰሩ አንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሃዋሳ ከተማ በስምንቱ ክፍለ ከተሞች በተለያየ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ከ100 የሚበልጡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማቶች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ዮናስ በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተቀናጀ ስራ ወደ ልማታዊ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ 16 ማህበራት መመረቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ማህበራቱ ባለፉት አምስት ዓመታት እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብና ለሌሎች በርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ወደ ልማታዊ ባለሃብትነት ለመሸጋገር በመብቃተቸው ለመመረቅ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ትናንት በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ከማህበራቱ በተጨማሪ ለእነዚህ ማህበራት ውጤታማነት በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዋንጫ፣ ሜዳሊያና ምስክር ወረቀት መሸለማቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተመራቂ ማህበራቱ መካከል አልሚ ትኩስ ወተት ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ባለቤት ወጣት አስማማው ታፈሰ በ1997 በብድር ባገኘው ሰባት ሺህ ብር ስራ መጀመሩን
 ገልጾ በአሁኑ ጊዜ ካፒታሉ ከ4 ሚልዮን ብር በላይ በመድረሱ ለ58 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡
ወጣት አስማማው ከመንግስትና ሌሎች አቻ ድርጅቶች በተደረገለት የተቀናጀ ድጋፍ በቀን ከ300 አርሶ አደሮች ወተት በመረከብ ለሁለት ሺህ ደምበኞች እንደሚያከፋፍል ተናግሯል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ከ21ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በ11ሺህ ማህበራት ተደራጅተው በተለያየ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር