POWr Social Media Icons

Tuesday, December 6, 2011

አዋሳ, ህዳር 26 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሲዳማ ዞን በበጀት አመቱ የመጀመሪያው ሩብ አመት ከ113 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ካፒታል ላስመዘገቡ 25 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የዞኑ ንግድና ኢንደስትሪ መምሪያ ገለጸ።
በመምሪያው የኢንቨስትመንት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለሀብቶቹ የሚሰማሩባቸው የስራ መስኮች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመሰማራት ነው።
በሩብ ዓመቱ ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በሁለት ባስመዘገቡት ካፒታል በ30 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንደነበረው ገልጸው ባለሀብቶቹ 3 ሺህ ሄክታር መሬት በማግኘታቸው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ከ4 ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
መምሪያው ለባለሀብቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው የተሰጣቸው ያላለሙና ለሌላ ሶስተኛ ወገን አሳልፈው የሰጡ 19 ባለሀብቶች የወሰዱትን ቦታ በመመለስ ፈቃዳችው እንዲሰረዝ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በዞኑ ወርቅ ታንታለምና የማእድን ውሃና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ሰፊ መሬት እንደሚገኝ ጠቁመው በመስኩ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
አዋሳ, ህዳር 26 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሲዳማ ዞን በወንሾ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በሽታና ድርቅን መቋቋም የሚችሉና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በቀለ ሁሞ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በወንዶ ገነት ደን ኮሌጅና በጅማ ግብርና ምርምር ተቋም በአዋዳ ማዕከል በምርምር የተገኙ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና በሽታና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሶስት ዓይነት የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡና ዝርያዎች እየተሰራጩ ነው።
በመሰራጨት ላይ የሚገኙት የቡና ዝርያዎች በሁለት አመት ጊዜ ምርት መስጠት የሚችሉና ከነባሩ የቡና ዝርያ ጋር ሲነጻጸር ከ8 እስከ 12 ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት በሄክታር መስጨት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው የቡና ዝርያ እስካሁን ከስድስት መቶ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች መሰራጨቱንና በሄክታር ከ20 እስከ 25 ኩንታል ምርት መስጠት እንደቻለ አቶ በቀለ ገልጸዋል።
በመጪው ሚያዚያ 2004 ለአርሶ አደሮች የሚሰራጭ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡና ችግኝ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመው በመንግስት ችግኝ ጣቢያ ብቻ የሚዘጋጀው የቡና ችግኝ በቂ ባለመሆኑ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ እንዲባዛ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቡና ችግኙን በማልማት ላይ ከሚገኙት አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አፀደ ጎኔሶ እንደገለጹት በምርምር ከተገኘው የቡና ዝርያ ለሙከራ ወስደው ካለሙት 700 ችግኝ ያገኙት ምርት ከፍተኛ በመሆኑ ችግኙን በብዛት ወስደው ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።