POWr Social Media Icons

Friday, September 30, 2011
Newየአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ ለሁለተኛ ጊዜ አዘቅት ውስጥ እየገባ መሆኑን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነው ቡና ገበያ እንዳያጣ መንግሥትና የቡና ነጋዴዎች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በመፈለግ ሥራ ላይ ተጠምደው ሰንብተዋል፡፡ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች እንዲሆኑ የተመረጡት ጃፓን፣ ቻይናና ሩሲያ ሲሆኑ፣ ለሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ የቆዩት በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ማርቆስ ተክሌ፣ አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድኑ መርተው ከትናንት በስቲያ ጃፓን ገብተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት  በጊዜያዊነት የወጣውን አዲስ ዕቅድ ማለትም የቡና ነጋዴዎች ከገበሬዎች ሰብስበው በምርት ገበያ በኩል ከሚቀርበው ቡና በተለየ ሁኔታ፣  በዩኒየኖችና  በኢንቨስተሮች የሚቀርበውን ቡና ጃፓን እንድትገዛ ለማግባባት ነው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው የቡና መጠን ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነውን ትገዛ የነበረችው ጃፓን፣ በቡና ውስጥ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችን አግኝቻለሁ በሚል ቡና ከኢትዮጵያ መግዛቷን በማቋረጧ ነው፡፡ የተቋረጠውን ግብይት ለማስጀመር ኢትዮጵያና ጃፓን ባለፉት ጊዜያት በጉዳዩ ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ጃፓን ኬሚካሉን ያገኘችው ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ከተላከ ቡና እንጂ፣ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ወደ ጃፓን ከተላከ ቡና ውስጥ አይደለም፡፡

ኬሚካል ተገኘበት የተባለው ቡና ደግሞ በጉዞና በተለያዩ ምክንያቶች ጃፓን እስኪደርስ ድረስ ስምንት ወራት የቆየ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ልትጠየቅ አይገባም የሚል መከራከርያ ቀርቧል፡፡

ይሁንና ጃፓን የኢትዮጵያን ቡና መግዛት በማቋረጥ ከቡና ውስጥ አራት ዓይነት የኬሚካል ይዘቶችን ስትመረምር ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሦስት ኬሚካሎችን በቡናው ውስጥ ባለማግኘቷ፣ ምርመራዋን በተቀረው የዲዲቲ ኬሚካል ላይ ብቻ እንደምታካሂድ ታውቋል፡፡ በዚህ ሒደት  እስከ የካቲት 2004 ዓ.ም  ድረስ ምርመራው እንደሚቀጥልና በቡና ላይ እስከዚህ ጊዜ ድረስ የዲዲቲ ኬሚካል  ካልተገኘ ምርመራው እንደሚቋረጥ  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በመግባታቸው፣ ኢትዮጵያ በትላልቅ ኢንቨስተሮችና በገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን የተመረቱ ቡናዎችን ለማቅረብ ከጃፓን ጋር መደራደሯን ቀጥላለች፡፡

ዲዲቲ የሚገኘው በገበሬዎች የተመረተ ቡና ውስጥ ብቻ ነው በሚል፣ ለጊዜው በኢንቨስተሮችና በዩኒየኖች የተመረተ ቡና ጃፓን እንድትገዛ መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው ሲሉ አንድ የቡና ኢንቨስተር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የልዑካን ቡድን ከአንድ ሳምንት በፊት በንግድ  ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ ያላ እየተመራ ወደ ቻይና ተጉዟል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የቡናን ጣዕም እያጣጣመ የመጣው የቻይና ገበያ በቀጥታ የኢትዮጵያን ቡና እንዲገዛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የሩሲያም ገበያ ለቡና አስፈላጊ ቢሆንም፣ ገበያው ግልጽ የሆነ አሠራር ስለሌለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሩሲያ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡፡

በኢትዮጵያ 12 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለቡና ልማት አመቺ ቢሆንም፣ ቡና እየለማ የሚገኘው ግን በ500 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ያህል መጠን መሬት በዓመት ከ250 ሺሕ ቶን በላይ ቡና የሚመረት ሲሆን፣ ለአገሪቱም ትልቁ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው ይኸው ምርት ነው፡፡

በ2003 የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ምርት ውስጥ ከ841.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም ደግሞ 528.3 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ የበጀት ዓመት ከዚሁ ምርት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ በመግባቱ ዕቅዱን እንዳያስተጓጉል በሚል ነው አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች እየተፈለጉ ያሉት ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ, መስከረም 18 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) - ጃፓን በኢትዮጵያ በሰብአዊ ደሕንነት ላይ ለሚካሔዱ ሁለት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል የ225 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ሰጠች፡፡

የገንዘብ ድጋፉን ለመስጠት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የጃፓን ኤምባሲ ከሲዳማ ዞን እና ሪሰሬክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት ከተሰኝ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን በጃፓን በኩል የፈረሙት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሒሮዩኪ ኪሽኖ፣ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እንዲሁ የሪሰሬክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎመንት ዳይሬክተር አቶ በላቸው ለማ ናቸው፡፡

የጃፓን መንግስት ለሰብአዊ ድህነነት ስራዎች ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን ድጋፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚው አምባሳደሩ ጠቁመዋል

ጃፓን ከ1997 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት፣ በመጠጥ ውሃና በሌሎችም መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎትን በሚያሟሉ ዘርፎች ከ300 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጓን አብራርተዋል፡፡

የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እና የሪሰሬክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎመንት ዳይሬክተር አቶ በላቸው ለማ በዚሁ ወቅት የገንዘብ ድጋፉን በአግባቡ ለተፈቀደለት ስራ በማዋል ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡