POWr Social Media Icons

Tuesday, February 22, 2011

ሃዋሣ, የካቲት 14 ቀን 2003 (ሃዋሳ) - የሃዋሳ ከተማን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ልማት ለማጥፋጠን በሚደረገው ጥረት የነዋሪዎችና የልማት በአጋሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡

የሃዋሣ 50ኛ ዓመትና ሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ቀን በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ ከ80 በላይ ግለሰቦችና ድርጅቶች የከተማው አስተዳደር ትናንት የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ወቅት ከንቲባው አቶ ሽብቁ ማጋኔ እንደገለፁት በዓሉ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የከተማውን ሁለንተናዊ ገጽታ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡

ከ80 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞችና ከ40 በላይ ድርጅቶች የተሣተፉበትን ይህንኑ በዓል ተከትሎ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት በእጅጉ መጨመሩን ገልፀዋል፡፡

በአሉ ሃዋሳ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ እንዲሁም የፈጣን ልማት፣ የእድገትና የአንድነት ተምሣሌት መሆኗን ማስመስከር የተቻለበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም ስኬት መላው ነዋሪ ህዝብና የልማት አጋሮች ያደረጉት ተሣትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ለበአሉ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ከ80 በላይ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትናንት ምሽት በተዘጋጀው ኘሮግራም ላይ ከከተማው ከንቲባ ከአቶ ሽብቁ ማጋኔ እጅ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ሃዋሳ, የካቲት 14 ቀን 2003 (ሃዋሳ) - በምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት አባል ሀገሮች ኢጋድ ድንበር ተሻጋሪ አካባቢ በሚኖሩ ህብረተሰብ መካከል የግጭት አፈታትና ሰላም ላይ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተጀመረ ።

በኢጋድ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ተቋም ከጀርመን መንግስት ጋር በመተባበር ለሦስት ቀናት በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ከኢትዮጵያ ፣ከኬኒያ ፣ ከሶማሌያ፣ከጅብቲ፣ከሱዳንና ኡጋንዳ ድንበር ተሻጋሪ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ተወካዮች መሳታፋቸውን የተቋሙ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር ሚስስ ትእግስት ሀይሉ ገልፀዋል ።

ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው በግጭት አፈታት ፣በሠላም ፣በልማትና ሌሎች የጋራ ስምምነትና ጥቅሞች ላይ የየአካባቢያቸውን ምርጥ ተሞክሮ በተናጥልና በቡድን በማቅረብ የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ።

የምርጥ ተሞክሮና የልምድ ልውውጥ መድረኩ በፊልምና በተዘጋጁ የሬዲዮ ድራማዎችና የእርስ በርስ ባህላዊ ግንኙነቶች ላይ በተደገፈ ፕሮግራም የሚካሄድ መሆኑን ገልጠዋል ።

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው ።

በአውደ ጥናቱ ላይ የየሀገሪቱ መንግስታትና የመስተዳድር ተወካዮች አጋርና መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳተፈዋል ።