ንግድ ሚኒስቴር የአራት ወራት የቡና ኤክስፖርት አሳስቦኛል አለ


-    ቡና ላኪዎች ይሻሻልልን ያሉትን መመርያ ሳይቀበለው ቀረ
‹‹በብትን ብትልኩ አንቀበልም ብለውናል›› ቡና ላኪዎች
‹‹በብትን የሚላከው በጃፓን ገበያ የደረሰብንን ካየን በኋላ ነው›› አቶ ያዕቆብ ያላ
 ንግድ ሚኒስቴር ባለፉት አራት ወራት የቡና ኤክስፖርት አፈጻጸምን በተመለከተ ከላኪዎች ጋር ባካሄደው ስብሰባ፣ ሊላክ ከሚገባው ቡና በታች በመላኩ እንዳሳሰበው አስታወቀ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ ያላ ላኪዎችን ጠርተው እንመካከር ባሉበት ህዳር 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ስብሰባ ላይ እንዳስታወቁት፣ በአራት ወራት ውስጥ ሊላክ የሚገባው ቡና ባለመላኩ ሰባት ወራት ብቻ ለቀረው የበጀት ዓመቱ ኤክስፖርት አፈጻጸም አሳሳቢ ነው፡፡

‹‹የቀረን ሰባት ወር ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከቡና 1.1 ቢሊዮን ዶላር እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ የአገሪቱ ዕቅድ ነው፡፡ ችግሮቹ በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ ይህንን ሁኔታ ይጐዳሉ፤›› በማለት አቶ ያዕቆብ አሳስበዋል፡፡ ለዓለም ገበያ መቅረብ ይገባው የነበረው የቡና መጠን የቀነሰው በተለያዩ ችግሮች መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ በተለይ ቡና በብትን እንዲላክ በወጣው መመርያ መሠረት ለመላክ ባለመቻላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ላለፉት አራት ወራት ለውጭ ገበያ ይላካል ያለው የቡና መጠን ከ66,400 ቶን በላይ ነበር፡፡ ነገር ግን የተላከው ቡና ከ44,029 ቶን በላይ ባለመሆኑ ከ22,371 ቶን በላይ ቡና ሳይላክ ቀርቷል፡፡ በጥቅምት ወር መላክ የነበረበት 75 ሺሕ ቶን ቢሆንም፣ ሊሰበሰብ የተቻለው 13 ሺሕ ቶን ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ወደ ውጭ የተላከው አራት ሺሕ ቶን ብቻ ይሆናል፡፡

ቡናው እንደታሰበው ሊላክ ያልተቻለው ደግሞ ቡናው በውል ከተሸጠ በኋላ በወቅቱ ሊላክ ባለመቻሉ (የተሸጡ ኮንትራቶች ስላልተፈጸሙ)፣ በምርት ገበያና በኒውዮርክ ገበያ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት፣ በላኪዎች መካከል የተፈጠረ አላስፈላጊ ውድድር፣ የዓለም የገበያና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በምክንያትነት አቅርቧል፡፡

ላኪዎች በአራት ወራት ውስጥ እንልከዋለን ያሉትን ቡና ሳይልኩ ቀርተዋል፣ በርካታ ቡና ተከማችቶ ተቀምጧል ያለው ሚኒስቴሩ፣ ቡና በብትን በኮንቴይነር (በከረጢት ውስጥ እዚያው ተበጥሮ ወደ ኮንቴነር መገልበጥ) የመላኩ እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት አኳያ ጨምሯል ብሏል፡፡ ዘንድሮ ከ6,454 ቶን በብትን ሲላክ አምና 4,700 ቶን ብቻ ተልኳል ያለው ሚኒስቴሩ፣ ከህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም ላኪዎች ቡናቸውን ሙሉ በሙሉ በብትን በኮንቴይነር እንዲልኩ የሚያሳስብ መመርያ አውጥቷል፡፡

ቡና ገዥዎቻችን በብትን ስንልክላቸው አንቀበልም ብለውናል፣ አንዳንዶቹም እስከ መሳደብ ደርሰዋል ያሉት ላኪዎች፣ መመርያው ይሻሻልልን በማለት የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርበው ነበር፡፡

ቡና ገዥዎቹ የውጭ ኩባንያዎች ቡና በብትን አንገዛም በማለታቸው የሚላከው የቡና መጠን ሊቀንስ እንደቻለና ወደፊትም ከፍተኛ የኤክስፖርት ጉድለት ሊከሰት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ቡና ገዥዎች በብትን ላለመግዛት ከሚያቀርቡት ምክንያት መካከል፣ አንዳንዶቹ ቡና ገዥዎች መልሰው ለትንንሽ ገዥዎች በችርቻሮ የሚሸጡት በመሆኑ፣ ከነጆንያው ካልተላከላቸው አንቀበልም እያሉ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ለትንንሾቹ ነጋዴዎች ልዩ ልዩ ቡና በአንድ ኮንቴነር ውስጥ ሲላክላቸው የቆየ ቢሆንም፣ በአዲሱ የብትን አላላክ መመርያ መሠረት ይህ የማይቻል ከሆነ ችግር ውስጥ እንወድቃለን በማለት ላኪዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአንጋፋዎቹ ቡና ላኪዎች መካከል አንዱ የሆኑት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ሲናገሩ፣ ከጃፓን እስከ አሜሪካ ያሉ ደንበኞቻቸው በኮንቴይነር በብትን እንዲላክላቸው እንደማይፈልጉ እንደነገሯቸውና የየአገሮቹን ደንበኞቻቸውን ምክንያትም ዘርዝረዋል፡፡

ጃፓኖቹ ከማሸጊያው ጀምረው ቡናውን በመመርመር ከኬሚካል ንክኪ ንፁህ መሆኑን ለማረጋገጥ ስለሚፈልጉ በብትን አይፈልጉም ያሉት መቶ አለቃ ፈቃደ፣ ሳዑዲዎችም ቡና የሚቆላ ኩባንያ ስለሌላቸው በብትን መግዛት አንፈልግም ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአውሮፓና የሲንጋፖር እንዲሁም የሌሎች አገሮች ደንበኞቻቸው ተመሳሳይ አቋም ስላላቸው በብትን የሚልከው በብትን እንዲልክ፣ በጆንያ የሚልከው በጆንያ መላክ እንዲችል ይፈቀድ ብለው ነበር፡፡

ሲንጋፖር በዓለም ላይ ከፍተኛው የኮንቴይነር ማስተናገጃ ተርሚናልና ሀብት ያላት አገር ብትሆንም፣ ከኢትዮጵያ ቡና ለመግዛት ቢሮ የከፈቱት በቅርብ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም ከፓፓዎ ኒው ጊኒና ከሌሎች አገሮች የገዙትን ቡና መልሰው ለጃፓንና ለመሳሰሉት አገሮች ሲሸጡ ቢቆዩም፣ በኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በብትን መግዛት እንደማይፈልጉ መቶ አለቃ ፈቃደ ተናግረዋል፡፡

ገዥዎቹ ዘለፋ መጀመራቸውን፣ ስለማሸጊያው እናንተ ምን አገባችሁ፣ በምንፈልገው ታሽጎ እንዲላክልን ምርጫው የእኛ ነው፣ ደግሞስ ድሆች ሆናችሁ መላኪያውን የምታማርጡት እናንተ ማን ናችሁ እየተባልን ነው የሚለውን የላኪዎቹን አቤቱታ፣ ሚኒስትር ዴኤታው የተመለከቱት ከሌላ አቅጣጫ ከመሆኑም በላይ፣ “በድህነታችን እንዲሳለቁብን አትፍቀዱላቸው፤ እናንተም የተሻላችሁ መሆናችሁን አሳዩ፤” በማለት አሳስበው በብትን መላኩን ግን ግፉበት ብለዋቸዋል፡፡

አሁን ባለው አሠራር እንዲቀጥልና በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይገባበት፣ እንደ አምስቱ ዓመት ዕቅድ ቀስ በቀስ እየጨመረ ይኬድበት እንጂ መቶ በመቶ በዚህ ዓመት መባሉ ይቅር፣ የሚሉትና መሰል የመፍትሔ ሐሳቦች ከላኪዎቹ ቀርበውም ነበር፡፡

እነኚህ የመፍትሔ ሐሳቦች ቢቀርቡም ንግድ ሚኒስቴር ሊለሳለስ ሳይችል ቀርቷል፡፡ “በወጣው መመርያ ቀጥሉና እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ያለውን አፈጻጸም ካየን በኋላ መልሰን በመገናኘት ውጤቱን እንገመግማለን፤” ያሉት አቶ ያዕቆብ፣ ‹‹እኛ በደሃ አቅማችን አበጥሮ የሚሞላውን ማሽን (ብሎወር) ከገዛንና ኮንቴይነር ካቀረብን፣ እነሱ ለምንድን ነው ትንሽ ፈቅ የማይሉት? ከኬሚካል ለማፅዳት ጆንያ ስናቃጥል፣ ላቦራቶሪ ስናቋቋም የነበረው ለእናንተው የጥራት ፍላጎት ነው እያላችሁ በአንድ ቋንቋ ተናገሩ፤›› በማለት ማሳሰቢያ አዘል አደራ ለላኪዎቹ ሰጥተዋል፡፡ ምንም እንኳ በመመርያው ላይ በግልጽ ባይሰፍርም፣ ከአንድ ኮንቴይነር በታች ለሚልኩ ልዩ ልዩ ቡና መላክ ለሚጠበቅባቸው የተለየ አስተያየት እንደሚደረግ ለላኪዎቹ ቃል ተገብቷል፡፡

አንዳንድ የመርከብ አገልግሎት ሰጪዎች የኮንቴነር አቅርቦት ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ለሪፖርተር ቢናገሩም፣ ንግድ ሚኒስቴር አያሳስብም በማለት ጥሩ አቅርቦት እንዳለው በመግለጽ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ዓርብ ሰብስቦ ካነጋገራቸው የቡና ገዥዎቹ ወኪሎችም ከ15ቱ አንዱ ብቻ በብትን ቢላክ ችግር እንደሌለበት ሲገልጹ፣ የቀሩት 14ቱ ግን በብርቱ ተቃውመውል፡፡

በብትን ቡናን መላኩ ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ የተወሰኑ ገዥዎችም ከገበያ ሊወጡ እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ ያዕቆብ፣ ‹‹ጥሎ የሚሄድ አይኖርም፣ ካለም አምስትና አሥር እጁ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በቀላሉ ሊሞላ የሚችል ክፍተት ነው፤›› ብለውታል፡፡ ከላኪዎቹ ባሻገር በሁሉም ቡና ተቀባይ አገሮች ያሉ ኤምባሲዎች የማሳመንና የማስተባበር ሥራ ለመሥራት መመርያ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡

ላኪዎች ከመመርያው ባሻገር የታገዱት የዘርፉ ተዋናዮችም ለኤክስፖርት ቡናው መቀነስ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ቢገልጹም፣ ንግድ ሚኒስቴር የሚቀበለው ምክንያት አልነበረም፡፡ የዕርምጃው መካረር ‹‹የቆየ ላኪ አይወደድም፤›› እንዲሉ ቢያስገድዳቸውም አቶ ያዕቆብ በጥብቅ አስተባብለውታል፡፡

በብትን ቡና እንዲላክ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረው በ1988 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ያኔ ዕውቀቱና ዝግጅቱ ስላልነበር አገር ይጎዳል ተብሎ ቀርቶ እንደነበር ላኪዎቹ አስታውሰዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር