ቡና በብትን እንዲላክ የወጣው መመርያ ነጋዴዎችን አደናግጧል


ከኅዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በንግድ ሚኒስቴር የወጣው መመርያ፣ ቡና በብትን በኮንቴይነር እንዲላክ የሚያሳስብ ነው፡፡
ቡናው በብትን መላኩ የሚያመጣው ጠቀሜታ ቢኖርም አነስተኛ ላኪዎችን፣ የቡና ደረጃዎችንና በይበልጥ ደግሞ የውጭ አገር የቡና ገዢዎችን ነባራዊ ሁኔታና ፍላጎት ከግምት ያላስገባ መሆኑን በመጥቀስ ነጋዴዎች ተችተውታል፡፡ አንዳንዶችም በአጠቃላይ የአገሪቱ የቡና ኤክስፖርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን በመግለጽ መመርያው በቶሎ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

ነጋዴዎች ከዚህ ቀደም በጆንያ እየሞሉ በኮንቴነር የሚልኩበት አሠራርን በብትን ኮንቴይነሩ ውስጥ በሚዘጋጅ የብትን ቡና መሙያ ከረጢት ተዘጋጅቶለት እንዲላክ በመመርያ መወሰኑ አንዳንድ ነጋዴዎችን አስደንግጧል፡፡ አንዳንዶችም በጆንያ የላኩት ቡና ከጂቡቲ ወደብ ተመላሽ እንደተደረገባቸው ለሪፖርተር የደረሱ ጥቆማዎች ያመለክታሉ፡፡

የቡና ጥራት መጓደል እንደ ጃፓን ያለውን ሰፊ ገበያ ካሳጣ በኋላ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ቆይቶ፣ ለጥራት ብቻ ሳይሆን ለቡና ደኅንነትና ለወጪ ቁጠባ ተገቢ ነው ያለውን የቡና አላላክ ዘዴን በመመርያ ለውጧል፡፡

ቡና በብትን ቢላክ ሊያስገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመተንተን የብትን ቡና አላላክን የሚያቀነቅኑት አቶ ግርማ ቡታ ናቸው፡፡ በአካካስ ሎጂስቲክስ ኩባንያ የኤክስፖርትና የመርከብ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ፣ ምንም እንኳ በብትን ቡናን መላኩ በሌላው ዓለም የተለመደና ኢትዮጵያ እጅግ ኋላ የቀረችበት ቢሆንም፣ ንግድ ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሳያወያይ መመርያውን ማውጣቱ በተለይ በጆንያ መላክ ያለባቸውን ነጋዴዎች እንደሚጐዳቸው አስረድተዋል፡፡

በብትን መላክ ማለት በኮንቴይነር ውስጥ በሚዘጋጅ ትልቅ የከረጢት አምሳያ ውስጥ በአንድ ጊዜ የሚዘረገፍበት አሠራር ሲሆን፣ በጆንያ ከሚላከው አኳያ እስከ አራት ኩንታል ተጨማሪ ቡና ለመላክና የቡና ጥራት እንደተጠበቀ ለማድረስ የሚያስችል አሠራር ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የባዶ ኮንቴይነር አቅርቦት እንደልብ በሌለበትና ቡናውን በብትን ለመሙላት የሚያስችሉ ማሽኖች (ፊለርስ) በብዛት በማይገኙበት ሁኔታ መመርያው መውጣቱ ተገቢ ሆኖ አላገኙትም፡፡

‹‹200 ሺሕ ቶን እንላክ ቢባል ያንን የሚያስተናግድ ኮንቴይነር አለ ወይ?›› ያሉት አቶ ግርማ፣ ቡና ላኪውን በብትን እንዲልክ ብናስገድደው እንኳ የውጭ ገዢውን ማስገደድ የማይቻል በመሆኑ ይህንንም ከግምት ማስገባት ይገባ እንደበር ገልጸዋል፡፡

‹‹ሁሉም ቡና ገዢ እኩል አይደለም፡፡ የቡናው ደረጃና የጥራቱም ነገር የተለያየ በመሆኑ ሁሉንም በአንድ ላይ በብትን መላክ አይቻልም፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣ ይልቁንም አነስተኛ ገዢዎች ወይም ላኪዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ በብትን በብዛት የሚልኩትም ለብቻቸው ተለይተው እንዲልኩ ቢደረግ ይሻል እንደነበር አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ቡና በብትንና በጆንያ እንዲላክ መፍቀድ አለበት ያሉት አቶ ግርማ፣ በብትን ብቻ ይላክ ብሎ ማስገደድ በጆንያ የሚላከውን ለማገድ እንዳልቻለና አሁንም እየተላከ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በጉና የንግድ ሥራዎች ኩባንያ የእርሻ ግብይት መምርያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኃይለ በርሃ ክንፈ በበኩላቸው፣ ቡና በብትን መላኩ የሚሰጣቸውን ጠቀሜታዎች በመዘርዘር በከፍተኛ ደረጃ መላክ ለሚችሉት እፎይታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮንቴይነር 18 ቶን ቡና በአንድ ትልቅ ከረጢት በአንድ ጊዜ መላክ መቻል የቡናን ጥራትና የቅሸባውን ስጋት ከመቀነሱም በላይ፣ ለአንድ ጆንያ የሚከፈለውን 36 ብር ያህል ወጪ እንደሚያስቀር ተናግረው፣ ትንንሽ ላኪዎች በጆንያ እንላክ ማለታቸው ሙሉ ለሙሉ በአንድ ጊዜ ይከላከላል የሚል ግምትእንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

መመርያው ከወጣ በኋላ ትንንሽ የቡና ትዕዛዞችን ከውጭ ተቀብለው መላክ ይችሉ እንደሆን ንግድ ሚኒስቴርን ጠይቀው፣ እንዲልኩ ስለተፈቀደላቸው መላካቸውን ተናግረዋል፡፡ ለሌሎችም እንዲህ እንደሚደረግ እምነት አላቸው፡፡ በብትን መላኩ የሚሰጣቸው ጥቅሞች ቢኖሩም፣ እንደ አቶ ግርማ ሁሉ የባዶ ኮንቴይነር አቅርቦትና የሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች መሟላት መሠረታዊ ጥያቄነት ላይ አያቅማሙም፡፡

አንድ ኮንቴይነር በትንሹ 30 ጆንያ ይይዛል ቢባል አንድ ነጋዴ በጆንያ ለመላክ ከ100 ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ያወጣል፡፡ አውሮፓውያኑ ገዢዎች ደግሞ ቡናውን ከመርከብ ለማውረድ፣ ለሰው ጉልበት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃቸዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ጆንያውን ለማስወገድ የሚቸገሩ በመሆኑ በብትን የሚላከውን ቡና ይፈልጉታል ብለዋል፡፡

የብትን ቡናን ጥቅም በእንዲህ ዓይነት ያብራሩት አቶ ግርማ፣ ከአንዳንድ አውሮፓውያን ገዢዎች ፍላጐት ባሻገር ባዶ ኮንቴይነር እንደልብ አለመገኘቱ፣ ሲገኝና ለላኪዎች ሲሰጥም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለኮንቴይነር የሚያስከፍለውን የመያዣ ሒሳብ አልመልስ እያለ ደንበኞችን ማስከፋቱን አስረድተዋል፡፡

ባዶ ኮንቴነር በአሁኑ ወቅት በብዛት የሚገኘው በየሁለት ወሩ ብቅል ከሚያስመጡ ቢራ ፋብሪካዎችና ከአንዳንድ ትንንሽ አስመጪዎች ነው፡፡ የደረቅ ወደብ ተገልጋይ ከሆኑት ከቢጂአይ፣ ከበደሌና ከሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካዎች የሚገኘው ኮንቴይነር 1000 ብር እየተከፈለበት መልሶ የወጪ ዕቃ ይታሸግበታል፡፡ ከጂቡቲ ወደብ ይምጣ ቢባል በኩንታል 85 ብር ታሳቢ እየተደረገ የ400 ኩንታል ዋጋ ተቆርጦለት ለባዶ ኮንቴይነር መክፈል ግድ የሚል በመሆኑ አማራጭ እንደማይሆን የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ፡፡

ጥቅሙ እንደሚያይል የሚነገርለት የብትን አላላክ መሠረተ ልማቱ ሳይሟላና የውጭ ገዢዎችን ፍላጐት ከግምት ሳያስገባ መመርያ መውጣቱ ንግድ ሚኒስቴር የብዙዎች ነጋዴዎች ዓይን እንዲያርፍበት ያስገደደ ሲሆን፣ በነገው ዕለት በጠራው የኤክስፖርት ዘርፍ ውይይትም ይህ ጉዳይ ዋና መነጋገርያ እንደሚሆን ነጋዴዎች እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ንግድ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ለማድረግ ቢሞከርም አልተሳካም፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር