የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ከ100 የሚበልጥ የምርምር ፕሮጀክቶች እያካሄደ ነው





አዋሳ, ህዳር 28 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ችግር ፈቺ የሆኑ ከ100 የሚበልጡ የምርምር ፕሮጀክቶች እያካሄደ መሆኑን የዩኒቨርስቲው የምርምር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገለጹ።

ዳይሬክቴሩ ዶክተር ተስፋዬ አበበ ሰሞኑን በሀዋሳ ከተማ በተካሄደ የምርምር ስራ ግምገማ አውደ ጥናት ላይ እንዳስታወቁት የምርምር ፕሮጀክቶቹ በተለይ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የልማት ፕሮግራም ስኬት የበኩላቸውን አሰተዋጾኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡
ቀደም ብሎና ዘንድሮ የተጀመሩት የምርምር ፕሮጀክቶች በግብርና ፣ በተፈጥሮ ሀብት ፣ በደን ልማት ፣ በእንስሳት ልማት፣ በጤናና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የምርምር ስራዎቹ የሚካሄዱት ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማና ዙሪያ፣ በቦርቻ ፣ በወንዶ ገነት፣በዳሌ ፣በሃገረ ሰላምና ሌሎች አካባቢዎች መሆኑን ጠቁመው በዩኒቨርስቲው የሚያስተምሩ የየዘርፉ ምሁራንና ተመራቂ ተማሪዎችን በማንቀሳቀስና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሁሉንም የልማት መስኮችን የዳሰሱ ችግር ፈቺ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡
በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በግብርናው ዘርፍ ለዝናብ አጠር አካባቢ ተስማሚና ውጤታማ የሆኑ አዳዲስ የበቆሎ የእንሰት ፣የስራ ስርና ሌሎች የምግብ ሰብል ዓይነቶች በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ለማድረስ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዜዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው የመማር ማስተማሩን ስራ በጥራትና በፍትሃዊነት ከማራመድ ጎን የሚካሄደው ምርምር ከውጪ ሀገራት መሰል የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸዋል።
ምርምሮችን በማስፋትና ግኝቶችን ወደ ምርት ስራ በማሸጋገር የተሻለ ለውጥና ዕድገት ለማምጣት በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ ማስታወቃቸውን የዩኒቨርስቲው ማርኬትንግና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር