በብሔራዊ ባንክ ብቻ ይሰጥ የነበረው የወርቅ ግዥ ሥርዓት በሐዋሳ መስጠት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ, መስከረም 18 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) - በብሔራዊ ባንክ ብቻ ይሰጥ የነበረው የወርቅ ግዥ ሥርዓት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በክልል አራት ከተሞች አገልግሎት መሰጠት እንደሚጀመር የማዕድን ሚኒስትሯ አስታወቁ፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ የወርቅ አቅርቦት መጠን እየጨመረ በመመጣቱ በብሔራዊ ባንክ ብቻ ይሰጠው የነበረውን ግዥ ወደ ምርት አካባቢዎች ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ወርቅ ከሚመረትባቸው ክልሎች መካከል በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በመቀሌና በአሶሳ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ግዥውን ሥርዓቱ ከሚቀጥለው ሳምንት በይፋ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ሰባት ቶን የነበረ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት ግን ምርትና አቅርቦቱ ከ13 ቶን በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

በክልሎች የወርቅ ግዥ ጣቢዎች መክፈት ወርቅ አቅራቢዎች ወደ አዲስ አበባ ያደርጉት የነበረውን ረጅም ጉዞ ከማስቀረቱ ባሻገር፤ ፈጣንና ቀልጣፋ የግዥ ሂደት ለመፍጠር እንደሚያስችል ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ወርቅ አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራት በአቅራቢያቸው ወርቅ የሚሸጡባቸው የግዥ ማዕከላት ባለመኖራቸው ለሌላ ገዢ በመሸጥ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸን ወይዘሮ ስንቅነሽ ገልጸዋል፡፡

በአራቱ ከተሞች የግዥ አገልግሎቱ ሲጀመር ግን የወርቅ አቅራቢዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል፡፡

በክልል ከተሞች በሚካሄደው የወርቅ ግዥ ሥርዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በአዲስ አበባ ማዕከል የሚሰጡትን ዓይነት አገልግሎት እንደሚሰጡም ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡

በነዚህ የግዥ ጣቢያዎች የወርቅ ዋጋም አዲስ አበባ ውስጥ በማዕከል ከሚገዛበት ዋጋ ተመሳሳይና አንድ ዓይነት እንደሚሆን በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

በቅርቡም ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ ዕደ ጥበባት ግብዓትነት የሚያገለግል ጥሬ ወርቅ የሽያጭ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተመልክቷል፡፡

በሚኒስቴሩ የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ማስተባበሪያ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ታምራት ሞጆ በበኩላቸው የወርቅ ግዥ ጣቢያ በክልሎች መከፈቱ ፍትሃዊ የሆነ የግብይት ሥርዓት ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው አብዛኛው ወርቅ በባህላዊ መንገድ የሚመረት ደለል ወርቅ መሆኑንናበአቅራቢያቸው የግዥ ጣቢያ መቋቋሙ አምራቾችና አቅራቢዎችን የሚያበረታታ ነው ማለታቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር