በሀዋሳ ከተማ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ስራ አከናወኑ

አዋሳ, ነሐሴ 30 ቀን 2003 (ሃዋሳ) - በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ወራት በተካሄደ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልገሎት ከሁለት ሚልዮን ብር የሚበልጥ ግምት ያለው ስራ መሰራቱን የከተማው ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ገለጸ፡፡

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ ትናንት በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ ምክትል መምሪያ ሃላፊው አቶ በላይ ዲካ እንደገለጹት በከተማው ስምንት ክፍለ ከተሞች 36 ሺህ 155 ወጣቶች ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ስምንት ሺህ 903 ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ወጣቶቹ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ችግኝ ተከላ፣ በጤና፣ በአረጋውያንና ወላጅ አልባ ህፃናት ድጋፍ ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦ 2 ሚልዮን 57 ሺህ 150 ብር መገመቱን አስታውቀዋል፡፡

ወጣቶቹ ከራሳቸውና ሌሎች ወገኖች አልባሳትና የፅህፈት መሳሪያ በማሰባሰብ ለ3 ሺህ 160 አረጋውያንና ወላጅ አልባ ህፃናት ከማከፋፈላቸው በተጨማሪ የስምንት አረጋውያንን መኖሪያ ቤት መጠገናቸውን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ሃላፊና የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ እንዳሉት ወጣቶቹ በእረፍት ጊዜያቸው ያበረከቱት አገልግሎት ለማህበረሰቡ ካስገኙት ጠቀሜታ በተጨማሪ የህይወት ክህሎት ትምህርት የቀሰሙበት ነበር፡፡

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ታዬ ቢሊሶ በከተማው እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ ቀጣይ እንዲሆን ወጣቱ በበጎ ፈቃድ አገልገሎት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበው የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ ለሆኑ ወጣቶችና ድጋፍ ላደረጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር