በዓይነቱና በይዘቱ ለየት ያለ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ በሐዋሳ ልገነባ ነው።


በዓይነቱና በይዘቱ ለየት ያለውን ዘመናዊ የሐዋሳ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ ለማስጀመር የተካሄደው የማስታወቂያ ፕሮግራም ሳምንታትን አስቆጥሯል፡፡ስራውን በተግባር ለመጀመር አንድ ነገር ቀርቶ ነበር፡፡ የሁለገብ ስታዲየሙን ግንባታ ገቢ አሰባሳቢና አስተዳደር ምክር ቤትን ማቋቋም፡፡ እሱም ባለፈው እሁድ በሐዋሳ ሃይሌ ሪዞልት እውን ሆኗል፡፡ 
ምክር ቤቱ የተቋቋመው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የሐዋሳ ከተማ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አስተዳደሮች፣ ባለሐብቶች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ነበር፡፡
የምክር ቤቱን መቋቋም ተከትሎ ግንባታውን ለማስጀመር የገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ ምን ይሁን በሚለው ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሐዋሳ ስታዲየም ቴሌቶን 2003 በሚል ስያሜ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የስራውን በይፋ መጀመር አብስረዋል፡፡
ለሁለገብ ስታዲየሙ ግንባታ እውን መሆን የክልሉ ህዝብ ፣ ከአገር ውስጥ እና ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
28 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል ተብሎ የሚጠበቀው ሰታዲየሙ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሲሆን እስከ 45 ሺህ መቀመጫ ያለው የእግር ኳስ ሜዳ፣ ዘመናዊ የአትሌቲክስ መወዳደሪያ እና ሌሎች 16 ዓይነት የስፖርት ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል ሜዳ ያካትታል፡፡
ለግንባታው እስከ 700 ሚሊዮን ብር ሊጠይቅ ይችላልም ተብሏል፡፡ ይህ የከልሉ ህዝብ ታሪክ የሆነው ስታዲየም ግንባታ የ56ቱም ብሄረሰቦች መገለጫ ሙዚየም በመሆኑ የዞን እና ወረዳ አስተዳደሮችም ህብረተሰቡን በማሳተፍ የበኩላቸውን ድጋፍ ለመወጣት በቁርጠኝነት ለመስራት ዘግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር