በሃዋሳ ከተማ ባሉ የገበያ ማዕከላት እና ከማዕከላቱ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ እየተደረገ ያለው ለውጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማጉላት አንፃር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚያበረክቱ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ ለውጦቹ ከማህበራዊ ፋይዳቸው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጐላ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡


የሃዋሳ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉ የሃገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን የነዋሪው ቁጥርም እየተበራከተ መጥቷል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡
ከነዚህም መካከል በከተማው አንድ ተጨማሪ የገበያ ማዕከል በታቦር ክፍለ ከተማ በፋራ ቀበሌ የተቋቋመ ሲሆን ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያም ለውጥ ተደርጓል፡፡
አቶ ብርሃኑ ላታሞ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በከተማው አንድ የገበያ ማዕከል  ብቻ የነበረ በመሆኑ ራቅ ባሉ የከተማው ክፍሎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አዳጋች ሁኔታዎች ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የከተማው ክፍሎች ሲከናወኑ የነበሩ የጉልት እና የቆጪ ገበያዎች ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ ገበያ የተወሰዱ ሲሆን በቀድሞ ገበያ ቦታ ያላገኙ  እስከ 400 የሚደርሱ ነጋዴዎችም በአዲሱ ገበያ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የከተማው ክፍሎች ይከናወኑ የነበሩ የከብት ገበያዎች ወደ አዲሱ ገበያ የተሸጋገሩ ሲሆን ገበያው አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የእሮብ እና አርብ ቀናት በተጨማሪ በሳምንት ውስጥ ባሉ ቀናቶች ሁሉ አገልግሎቱ ይከናወናል ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በከተማው የተቋቋመው አዲሱ የገበያ ማዕከል በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ እና በመሰረተ ልማት እየተደራጀ እንደሚኝ አቶ ብርሃኑ ገልጸው፤ ገበያው አመቺ መንገድ የተዘረጋለት ከመሆኑ በተጨማሪም ወደ ማዕከሉ የሚደረግ ጉዞ ቀልጣፋ እንዲሆን 3 ማዕከላትን መሰረት ያደረገ የታክሲ እና የባጃጅ ስምሪት ተመድቦ ህብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
በከተማው ተግባራዊ ከተደረጉ ለውጦች መካከል በሰረገላ ጋሪዎች ላይ የተደረገው የስምሪት ወሰንና የጋማ ከብቶችን እንቅስቃሴ በተመለከተ የወጣው ደምብ አንዱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የሰረገላ ጋሪ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የአስፋልት መንገዶችን ከማቋረጥ ባለፈ ከውስጥ ለውስጥ መንገዶች በቀር በዋና የአስፋልት መንገዶች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ነው የተገለጹት፡፡
ይህም ተግባራዊ የተደረገው በተከማው የትራንስፖርት ፍሰትን ለመቆጣር መንገዶችን ከጥፋት ለመታደግ እንዲሁም የከተማውን ገጽታ ለመጠበቅ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል ሲል የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን  የሥራ ሂደት ዘግቧል፡፡


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር