በሲዳማ ዞን አርቤጎና ዳሎታ እና ሃገረ ሰላም ወረዳዎች የአሳ ጫጩት ማራቢያ ማዕከል እየተገነባ ነው

ሃዋሳ, ታህሳስ 10 ቀን 2003 (ሃዋሳ) -በደቡብ ክልል አሳን በብዛት ለማምረት በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የአሳ ጫጩት ማራቢያ ማዕከል እየተገነባ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ባለፉት ሶስት ወራት ከ3ሺህ ቶን በላይ አሳ ተመርቶ ለገበያ መቅረቡም ተገልጧል ።

በቢሮዉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን የስራ ሂት ባለቤት አቶ ብርሃኑ ጦፉ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጡት የአሳ ማራቢያ ማእከሉን መገንባት ያስፈለገዉ በእርባታዉ ለመሳተፍ የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ነዉ ።

የአሳ ማራቢያ ማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች የአሳ ጫጩት በማቅረብ ከሚሰጠዉ አገልግሎት በተጨማሪ ለአርሶ አደሩና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠትና በምርምር ማዕከልነት እንደሚያገለግል አስረድተዋል።

በክልሉ ዉሃ ገብ በሆኑ ደጋማ አካባቢዎች በአርሶ አደሮች ጓሮና በእርሻ ማሳ አካባቢ አነስተኛ የአሳ ማራቢያ ኩሬዎችን በማዘጋጀት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ሶስት አመታት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸዉን ተናግረዋል ።

በተለይም በሲዳማ ዞን አርቤ ጎና ፣ዳሎታ ፣ሃገረ ሰላም ወረዳዎች፣ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳና በሌሎችም አካባባቢዎች ከ100 የሚበልጡ ሰዉ ሰራሽ ኩሬዎችን በማዘጋጀትና ከ25ሺህ በላይ የአሳ ጫጩቶችን በመጨመር ከእርባታዉ ከ1ሺህ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል


የወላይታ ግብርና ምርምር ማዕከል አርሶ አደሮች ከመደበኛ የእርሻ ስራቸዉ ጎን ለጎን የተሻለ የስጋ ምርት የሚሰጡ የአሳ ዝርያዎችን በማራባት ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑም ተገልጧል ።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች አሳ ለምግብነት ያለዉን ጠቀሜታ እየተረዱ በመምጣታቸዉ ባለፉት ሶስት ወራት 14 አዲስ የአሳ ማራቢያ ኩሬዎችን ማዘጋጀታቸዉን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሶስት ወራትም ከክልሉ ሃዋሳ ፣ሻላና ፣አብያታ ሃይቆች እንዲሁም ከተለያዩ ወንዞችና ሰዉ ሰራሽ የአሳ ማራቢያ ኩሬዎች ከ2ሺህ50 ቶን በላይ አሳ ለማምረት ታቅዶ 3ሺህ94 ቶን ተመርቶ ለገበያ መቅረቡንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር