በሐዋሳ ቅ/ገብርኤል በተከሰተ ብጥብጥ ጉዳት ደረሰ፤ አዋኪዎቹ በፖሊስ ተይዘዋል

• ሁከቱ ሊቀ ጳጳሱ ወደተመደቡበት ሀገረ ስብከት እንዳይመጡ ለማሣቀቅ እና አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ችግር መፍታት እንደተሳናቸው ለማሳየት ጀምበር በጠለቀችባቸው በእነ ያሬድ አደመ የታለመ ነው፤
•‹‹በሁከቱ ስለት፣ ዱላ እና ድንጋይ የተጠቀሙት ወሮበሎቹ ባደረሱት ድብደባ ከአምስት ያላነሱ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ፖሊሶች ተጎድተዋል፤ አንዱ ወጣት ጆሮው የተቆረጠ ሲሆን በጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሌላው ወጣት ደግሞ ራሱን ስቶ በጉሉኮስ እየተረዳ ይገኛል፡፡›› (የሆስፒታል ምንጮች)
•ፖሊስ ከያሬድ እና ዓለምነህ ሽጉጤ በተጨማሪ በሁከቱ የተሳተፉ ሰባት ቀንደኛ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፤
•ፓትርያሪኩ፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና በጋሻው ደሳለኝ ሁከተኞቹን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረጉ ነው፤
•የሐዋሳ የአገር ሽማግሌዎች ዛሬ የክልሉን ርእሰ መስተዳድር እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል
• በመጪው ቅዳሜ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ወደ ሐዋሳ እንደሚመጡ በአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ሲነገራቸው ያጉረመረሙት ‹‹የተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› አባላት የሊቀ ጳጳሱ ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት እንደሚያስከፋቸው በአዎንታ አረጋግጠዋል
•‹‹እነያሬድ አደመ ተከልክለው ማንም አራት ጎማ ያመጣው ሁሉ በዚህ መድረክ ላይ አያዝበትም፡፡››
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 8/2010፤ ጥቅምት 29/ 2003 ዓ.ም) – ትናንት እሑድ ሰንበት ጥቅምት 28 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸቱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለማነጋገር የጠሩት ስብሰባ ዓለምነህ ሽጉጤ በሚባለው ግለሰብ በሚመራው ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማኅበር›› እየተባለ በሚጠራው አካል በታቀፉ እና በእነ ያሬድ አደመ በተደራጁ ወሮበሎች ከፍተኛ ሁከት ተቀስቅሶበት ውሏል፤ በሁከቱ ወደ ገዳሙ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዳይገቡ በወሮበሎቹ የተከለከሉት እና በቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከታገዱት ሕጋዊዎቹ የሰንበት ት/ቤቱ አባላት መካከል ከአምስት ባላነሱት ላይ በስለት፣ በበትር እና በድንጋይ በደረሰባቸው ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አንዱ ወጣት ጆሮው የተቆረጠ ሲሆን ሚስማር በተሰካበት ብትር ጭንቅላቱን የተመታው ሌላው ወጣት ደግሞ ራሱን ስቶ በሆስፒታል በጉሉኮስ እየተረዳ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡ የገዳሙን ዙሪያ በመክበብ እና ወደ ቅጽሩ በመግባት ብጥብጡን ያበረደው የፌዴራል ፖሊስ ሁከቱን ለመቀስቀስ ቅዳሜ ምሽት የጠብ ምክር ሲያቅዱ አድረው ረፋድ ላይ በመከሩት መሠረት ብጥብጡን ከለኮሱ በኋላ ኮንትራት በተነጋገረው ሚኒባስ ታክሲ ከሐዋሳ ከተማ ወጥቶ ለመሸሽ የሞከረውን ያሬድ አደመን እንዲሁም ዓለምነህ ሽጉጤን ከሌሎች ሰባት ግብረ አበሮቻቸው ጋራ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከሁለት ሰባክያነ ወንጌል እና ከሁለት ዘማርያን ጋራ ወደ ሐዋሳ በማምራት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና የትውውቅ መርሐ ግብር ያካሄዱት ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸቱ ሁከተኞቹን ጨምሮ ከሐዋሳ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአድባራት አስተዳዳሪዎች እና ከቀድሞው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሰበካ ጉባኤ አባላት እስከ ቅዳሜ ምሽት ድረስ እየተወያዩ ከመለስተኛ ዕንከኖች በቀር ሁኔታውን በትዕግሥት እና በትሑት ሰብእና ይዘው በመግባባት መንፈስ ለመዝለቅ ችለው ነበር፡፡ የትውውቁ መርሐ ግብር እና የስብከተ ወንጌሉ አገልግሎት ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በመጡት ሰባክያን እና ዘማርያን በጥሩ ሁኔታ መያዙ፣ ስምሪቱም በሀገረ ስብከቱ ማእከላዊ ቁጥጥር መደረጉ ያልተመቻቸው ያሬድ አደመ እና ዓለምነህ ሽጉጤም ቅዳሜ ማታ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አዳራሽ ተከታዮቻቸውን ይዘው በማግሥቱ እሑድ የጠብ መንሥኤ የሚፈጥሩበትን ስልት ሲቀይሱ አመሹ፤ እሑድ ከቀትር በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ግን ሥራ አስኪያጁ ለብቻቸው እንዲያነጋግሯቸው በጠየቁት መሠረት ለማድረግ ታቅዶ ለነበረው ውይይት አምስት ተወካዮቻቸውን ይዘው እንዲመጡ ቀጠሮ ተይዞላቸው ነበር፡፡
በውይይቱ ላይ አዲሱን ሥራ አስኪያጅ ከቃለ ዓዋዲው ውጭ ‹የተመረጡቱ› ሕገ ወጡ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር እና የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ አባላት በሐላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ለመጠየቅ ካልሆነም አካላዊ ጥቃት በማድረስ ጭምር ለማስገደድ ወስነው ነበር፡፡ ከቀትር በፊት ጠዋት ደግሞ ተኣምረ ማርያም የሚያነቡትን ካህን እና ከሥራ አስኪያጁ የልኡካን ቡድን አባላት አንዱ የሆነውን ዘማሪ ምንዳዬ ብርሃኑን ከመድረኩ ጎትቶ ለማውረድ አቅደው ነበር – ‹‹እነያሬድ አደመ ተከልክለው እነርሱ ባቀኑት አገር ማንም በአራት ጎማ የመጣ ሁሉ በዚህች መድረክ ላይ አያዝባትም!›› የሚል ማስጠንቀቂያ ከማፊያው ቡድን አባላት በአንዱ ተነግሮት ነበር – ዘማሪ ምንዳዬ፡፡
እሑድ ጠዋት ድርገት እንደ ወረዱ የዐዋኪው ቡድን አባላት የሆኑ ዘማሪ ነን ባዮች ዩኒፎርም ለብሰው መዘመር ይጀምራሉ፡፡ ሁኔታውን በትዕግሥት ያሳለፉት ሥራ አስኪያጁ የዕለቱ ተኣምር እንዲነበብ እና ስብከተ ወንጌሉ እንዲሰጥ ያደርጋሉ፡፡ በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የፊታችን ቅዳሜ እንደሚመጡ በመናገር ላይ እንዳሉ የቡድኑ አባላት ጉርምርታ ድምፅ ያሰማሉ፤ ሥራ አስኪያጁም የጉርምርምታው ምክንያት የመከፋት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲጠይቁ የአዎንታ መልስ ይሰጣቸዋል፤ አለ የሚባለውን ችግር በዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከአምስት ተወካዮቻቸው ጋራ በሚደረገው ውይይት በመነጋገር ለመፍታት መታቀዱን ያሳውቃሉ፡፡ አያይዘውም የቡድኑ አባላት ቅዳሴ ሳያልቅ እና ተኣምረ ማርያሙ ሳይነበብ መዝሙር መዘመራቸው አግባብ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፤ በዚህ ወቅት ከቡድኑ አባላት አንዱ መነጋገሪያውን በማንሣት፣ ‹‹ምእመናን ሁላችሁም ወደ አዳራሽ ግቡ›› በማለት ያዝዛል፡፡ ሥራ አስኪያጁም ጸሎተ ቅዳሴው የተጠናቀቀ በመሆኑ ምእመናን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት የሆኑ ወጣቶች ብቻ ወደ አዳራሽ እንዲገቡ ያሳስባሉ፡፡
ሥራ አስኪያጁ በሰጡት ማሳሰቢያ መሠረት ቀደም ሲል በነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና በሐዋሳ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አላግባብ በተሾሙት አስተዳዳሪ ውሳኔ የታገዱት ሕጋዊዎቹ የሰንበት ት/ቤት አባላትም ወደ አዳራሹ ለመግባት ሲሞክሩ እንዳልተፈቀደላቸው በማፊያ ቡድኑ ይነገራቸዋል፡፡ በዚህ መካከል በተፈጠረው ዐምባጓሮ በምክር ያደሩት እና ያሬድ አደመ በሞባይል ስልክ የሚመራቸው ወሮበሎች ሚስማር በተመታበት ብትር እና በድንጋይ እሩምታ ሽሽት የመረጡትን ወጣቶች መአት ያወርዱባቸው ጀምር፡፡ በድንጋዩ ውርጅብኝ መፈንከት ያልቀረላቸው እና ክሥተታቸው እንደ ተራዳኢ መልአክ የታየው የፌዴራል ፖሊስ አባላትም ሁኔታውን በቅርበት ይከታተሉት ኖሮ ድብደባውን በአስቸኳይ ባይቆጣጠሩት ጉዳቱ ሊባባስ ይችል እንደ ነበር የተነገረ ሲሆን የጉዳተኞችን መጠን አስመልክቶ የተለያየ አኀዝ ተዘግቧል፡፡ ለደጀ ሰላም በደረሰው ጥቆማ ከአምስት ያላነሱ ወጣቶች እና ፖሊሶች ጭምር መጎዳታቸው የተነገረ ሲሆን አንድ ወጣት እስከ አሁን ራሱን እንደ ሳተ በሆስፒታል ሕክምና ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
ትናንት ማምሻው ድረስ እና ዛሬ ጠዋት በጋሻው እና ወ/ሮ እጅጋየሁ በተለይም ያሬድ አደመን ለማስለቀቅ ጥረት ማድረጋቸው የተሰማ ቢሆንም ከመንግሥት ምንጮች እንደተሰማው ፖሊስ በቀጣይ ሁከቱን በማስተባበር እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩትን በጋሻውን እና ወ/ሮ እጅጋየሁን በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ይችላል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ሁከተኞቹን እንዲያስፈቱ ጫና እያደረጉባቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ ሲሉ ሀገረ ስብከቱን በአስነዋሪ ድርጊቶቻቸው እና የማያባራ በሚመስለው የእርስ በርስ መከፋፈል አዙሪት ውስጥ ባሰነበቱት በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በቀጠለው ምርመራ ለሁከት የሚያሰማሯቸው ኀይሎች ከያሉበት እየታደኑ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በሁኔታው ሲማረሩ የቆዩት የከተማው ምእመናን የጸጥታ ኀይሉ ከጥንተ ታሪካቸው ጀምሮ የሁከት መዝገብ እና የመለያየት አበጋዝ ሆነው የኖሩት ግለሰቦች በሚያሳዩት እስስታዊ ጠባይዕ ሳይዘናጋ ለአዲሱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር እና ለከተማው አጠቃላይ ሰላም ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ ጥብቅ እና ፍትሐዊ ርምጃ እንዲወስድባቸው ተማፅነዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር